Skip to main content

ኢትዮጵያ፡ መገናኛ-ብዙሃን በመጥፋት ላይ ናቸው

በግንቦት ወር ከሚካሄደው ምርጫ አስቀድሞ የህግ እና የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ ወሳኝ ነው

(ናይሮቢ ጃንዋሪ 22፣ 2015 ዓ.ም.) - የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ መገናኛ ብዙሃን ላይ በሚፈጽመው ስልታዊ ጫና ምክንያት ከግንቦት 2007ቱ ምርጫ አስቀድሞ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ ተስፋ አሰቆራጭ ሁኔታ ተፈጥሯል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ። ባለፈው ዓመት መንግስት የጥቃት ዘመቻ ካካሄደባቸው በኋላ ስድስት የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን ተዘግተዋል፣ ቢያንስ 22 ጋዜጠኞች፣ ጦማሪያን እና አሳታሚዎች በወንጀል ተከሰዋል እንዲሁም ከ30 በላይ ጋዜጠኞች አፋኝ የሆኑ ህጎችን መሰረት አድርጎ ሊፈጸምባቸው የሚችልን እስር በመፍራት ሃገር ለቀው ተሰደዋል፡፡

“’ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም’፡ የመገናኛ-ብዙሃን የመብት ጥሰት በኢትዮጵያ” በሚል የቀረበው ባለ 76 ገጹ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ነጻ ጋዜጠኝነትን እንዴት እንዳሽመደመደው በዝርዝር አቅርቧል፡፡ እ.ኤ.አ. ከግንቦት 2013 ዓ.ም. እስከ ታህሳስ 2014 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ወስጥ ከ70 በላይ በስራ ላይ ያሉ እና የተሰደዱ ጋዜጠኞችን ሂዩማን ራይትስ ዎች ቃለ-መጠይቅ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነታቸውን ስለተገበሩ ብቻ 19 ጋዜጠኞች እንዲታሰሩ እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ  ከ60 የሚበልጡ ሌሎች ደግሞ ሀገር ለቀው እንዲሰደዱ ያደረገውን የመንግስትን አንድ ወጥነት ያለው የጫና ማሳደር አፈጻጸም ሂደት መረዳት ለመረዳት ችሏል።

“የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ መገናኛ-ብዙሃንን ጠቃሚ የመረጃ እና ትንታኔ ምንጭ አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ የስጋት ምንጭ አድርጎ በመቁጠር በሃገሪቱ የሚገኙ ነጻ ድምጾች ላይ ስልታዊ በሆነ መንገድ ጥቃት ይፈጽማል::” ያሉት የሂዩማን ራይትስ ዎች  የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው “የኢትዮጵያ መገናኛ-ብዙሃን ለግንቦቱ ምርጫ ወሳኝ ሚና መጫወት አለባቸው፤ ነገርግን በርካታ ጋዜጠኞች የሚቀጥለው ጽሁፋቸው እስር ቤት ያስወረውረናል በሚል ስጋት ውስጥ ነው የሚገኙት።’’ ብለዋል።

አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ የህትመት፣ የቴሌቪዥን እና ሬድዬ ስርጭቶች በመንግስት ቁጥጥር ስር ናቸው፤  የቀሩት ጥቂት የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን የመዘጋት እጣ እንዳይደርስባቸው ከመፍራት የተነሳ በአሳሳቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለሚሰሯቸው ዘገባዎች ብዙውን ጊዜ በራሳቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ ያደርጋሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. የተዘጉት ስድስት ነጻ የህትመት መገናኛ-ብዙሃን በመንግስት ባለቤትነት በተያዘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ህትመቶቹ ከአሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አላቸው የሚል ውንጀላ ያለበት ዘገባን ጨምሮ ረዘም ላለ ጊዜ የማሸማቀቂያ ዘመቻ ሲካሄድባቸው ቆይቷል፡፡ ማሸማቀቂያው በህትመቶቹ የስራ ባልደረቦች ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ማድረስ፣ በማተሚያ ቤቶች እና አከፋፋዮች ላይ አሉታዊ ጫና መፍጠር፣ የፈቃድ አሰጣጥና እድሳትን ማዘግየት ብሎም በአዘጋጆቹ ላይ የወንጀል ህግ መመስረትን ያካትታል። በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰራተኞች ሃገር ለቀው ተሰደዋል፡፡ ሶስት የህትመት ባለቤቶች የወንጀል ህጉን በመጣስ ጥፋተኛ የተባሉ ሲሆን እያንዳንዳቸው ከሶስት ዓመት በሚበልጥ እስራት እንዲቀጡ በሌሉበት ተፈርዶባቸዋል፡፡ ለክሱ ማስረጃ ሆነው የቀረቡባቸው የመንግስት ፖሊሲዎችን በመተቸት ያተሟቸው ጽሁፎች ናቸው።

ጥቂት ከፍ ያለ ታዋቂነት ያላቸው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ስቃይ በስፋት የታወቀ ሲሆን በደርዘኖች የሚቆጠሩ በአዲስ አበባ እና በክልሎች የሚገኙ ሌሎች ጋዜጠኞች በደህንነት ባለስልጣናት ስልታዊ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል።

በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት ተመሳሳይ አካሄድ ያለው ነው ያለው ሂዩማን ራይትስ ዎች፤ ትችት ያዘሉ ዘገባዎችን የሚጽፉ ጋዜጠኞች ዛቻ ያለበት የስልክ ጥሪ እና የአጭር ጽሁፍ የስልክ መልዕክት ይደርሳቸዋል፤ እንዲሁም የደህንነት ባለስልጣናት እና የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ወደ ስራና መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ያስፈራሯቸዋል። አንዳንዶቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ እንደዚህ አይነት ማስፈራሪያዎች እንደደረሱባቸው ተናግረዋል፡፡ እንደእዚህ የአይነት ማስፈራሪያዎች ጸጥ ሊያሰኟቸው አሊያም በራሳቸው ላይ ቅደመ-ምርመራ እንዲያካሂዱ ሊሸማቅቋቸው ካልቻሉ አብዛኛውን ጊዜ ማስፈራሪያው የበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥላል አሊያም እስር ይከተላል፡፡ በአብዛኛው ከሽብር ጋር በተያያዙ ክሶች የጥፋተኝነት ውሳኔ የተላለፈባቸው እና ፍትሃዊ ያልሆነ እና በተራዘመ የፍርድ ሂደት ያለፉ ጋዜጠኞች የወንጀል ጉዳዮች ላይ የፍርድ ቤቶች ገለልተኛነት እመብዛም ነው ወይም ጭራሹንም የለም።

“ተገቢ ባልሆኑ የወንጀል ክሶች እና ሌሎች ማሸማቀቂያ መንገዶች ነጻ ድምጾችን በማፈን ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ጋዜጠኞች ከሚያስሩ ሀገሮች አንዷ እየሆነች ነው፡፡” የሚሉት ሌፍኮው “መንግስት ያለአግባብ የታሰሩ ጋዜጠኞችን ባስቸኳይ መፍታት አለበት እንዲሁም የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነትን ለመጠበቅ የህግ ማሻሻያ ማድረግ አለበት፡፡”ብለዋል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኞቹ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከመንግስት ጋር ትስስር ያላቸው ናቸው፣ መንግስት ከሚያራምዳቸው አቋሞች ብዙም አያፈነግጡም፤ እንዲያውም የመንግስት ፖሊሲዎችን ያስተዋውቃሉ፣ የልማት ውጤቶችን ያወድሳሉ፡፡ ከ80 በመቶ የሚበልጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠራማ አካባቢዎች በመሆኑ እና ሬድዮ እስከአሁን ድረስ ዋናው የዜና እና መረጃ ማግኛ ምንጭ ከመሆኑ አንጻር ሬድዮን መቆጣጠር ለፖለቲካው ከፍተኛ አስፈለጊነት አለው። የፖለቲካ ክስተቶችን የሚዘግቡ ጥቂት የግል ሬድዮ ጣቢያዎችም በአካባቢ የመንግስት ባለስልጣናት ስራዎቻቸው የሚታረሙበት እና ለስርጭት የቅድሚያ ፈቃድ የሚያገኙበት አሰራር አለ። ፈቃድ ካገኘው ይዘት  የሚያፈነግጡ አሰራጮች ጥቃትና ወከባ ይደርስባቸዋል፣ ይታሰራሉ፣ በበርካታ አጋጣሚዎችም ሃገር ለቀው ለመሰደድ ይገደዳሉ።

መንግስት በዲያስፖራ ባለቤትነት የተያዙ የውጭ የሬድዮ እና የቴሌቪዥን ስርጭቶች አየር ሞገዶችን በተደጋጋሚ ያፍናል፤ ድረ-ገጾቻቸውንም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ያደርጋል።፡፡ ለእነዚህ ብሮድካስተሮች የሚሰሩ ሰራተኞች ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርስባቸዋል፤ እንዲሁም የመረጃ ምንጮቻቸው እና በዓለም ዓቀፍ መገናኛ-ብዙሃን ቃለመጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል። እነዚህን ስርጭቶች የተመለከቱ ወይም ያዳመጡ ሰዎችም ጭምር ለእስር ተዳርገዋል፡፡

መንግስት የጋዜጠኞች ማህበራት ለመመስረት የሚደረግ ጥረትን በማደናቀፍ፣ ለግል መገናኛ-ብዙሃን የሚሰጥ ፈቃድ ወይንም እድሳትን በማዘግየት፣ ባሉት ጥቂት ማተሚያ ቤቶች እና አከፋፋዮች ላይ አሉታዊ ጫና በማሳደር እንዲሁም በመንግስት መገናኛ-ብዙሃን የስራ ቅጥርን ከገዢው ፓርቲ አባልነት ጋር በማያያዝ በርካታ በግልጽ የማይታዩ ግን ደግሞ ውጤታማ የሆኑ አስተዳደራዊ እና ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ገደቦችንም ስራ ላይ ያውላል።

ማህበራዊ ድረገጾችም ከፍተኛ ገደብ ይደረግባቸዋል፤ እንዲሁም በዲያስፖራዎች የሚመሩ በርካታ የኢንተርኔት ጦማሮች እና ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል። በሚያዚያ ወር ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁ እና በሃገሪቱ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በተለይ ለወጣት ኢትዮጵያዊያን ትንታኔ የሚያቀርቡ የኢንተርኔት ጦማሪያን ስብስብ አባላት የሆኑ ስድስት ጦማሪያንን መንግስት አስሯል። በሃገሪቱ የጸረ-ሽብር አዋጅ እና የወንጀል ህግ መሰረትም ክስ ተመስርቶባቸዋል። ከሌሎች ታዋቂ ጋዜጠኞች ጋር በአንድነት እየታየ የሚገኘው ክሳቸው ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን ሊያዛቡ የሚችሉ በርካታ ግድፈቶች ተስተውለውበታል። እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 14 የፍርድ ሂደቱ ለ16ኛ ጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቶበታል። ተከሳሾቹም ከ260 ቀናት በላይ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን እስር እና ክስ በተለይ ተችት የሚያቀርቡ ጦማሪያን እና የኢንተርኔት ላይ ተሟጋቾችን ጨምሮ በኢትዮጵያ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን አድርጓል።

እየጨመረ የመጣው መገናኛ-ብዙሃን ላይ የሚፈጸም አሉታዊ ጫና በግንቦት ወር በሚካሄደው ምርጫ የሚኖረውን የመገናኛ-ብዙሃን ይዞታ ያለጥርጥር ይጎዳዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች፡፡

“ከግንቦቱ ምርጫ አስቀድሞ መንግስት የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነትን በተመለከተ ከፍተኛ ማሻሻያ ለማድረግ አሁንም ጊዜ አለው::” ያሉት ሌፍኮው “አፋኝ ህጎችን ለማረም እና የታሰሩ ጋዜጠኞችን ለመፍታት የሚያስፈልገው የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንጂ ረጅም ጊዜ ወይንም ከፍተኛ ሃብት አይደለም፡፡” ብለዋል።

Your tax deductible gift can help stop human rights violations and save lives around the world.

Region / Country