Skip to main content

ኢትዮጵያ፡ በተቃዋሚዎች ላይ የሚደርሰው ጫና ተባብሷል

በግንቦት 2015 ዓ.ም ከሚካሄደው ምርጫ አስቀድሞ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አስከፊ ደረጃ ላይ ደርሷል

(ናይሮቢ፣ ጃንዋሪ 29 ቀን 2015ዓ.ም.) - የኢትዮጵያ መንግስት ተቃውሞን ለማፈን የሚያካሂደውን የእስር፤ የውንጀላ እና ህገ-ወጥ የሃይል እርምጃ ዘመቻ በ2014 ዓ.ም. አባብሶ ቀጥሎበታል ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ ይፋ ባደረገው የ 2015 የዓለም ሪፖርት አስታወቀ። መንግስት ለሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች የሚሰጠው ምላሽ ጥቃት፣ ማስፈራሪያ፣ እና የዘፈቀደ እስር ነው፤ ጋዜጠኞችን እና ተቃዋሚ ተሟጋቾችን እንዲሁም በመንግስት ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ወገኖችን በተለይ ለመጫን አፋኝ ህጎችን ተጠቅሟል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግስት በ2014ም የተቃውሞ ምልከቶችን ለማዳፈን ከዚህ በፊት ሥራ ላይ ውለው ውጤታማ የነበሩትን እርምጃዎች ወደ መውሰድ ተመልሷል”። ያሉት የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው “ጋዜጠኞች እና ተቃዋሚዎች የበለጠ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ይህም ከግንቦት 2015ቱ ምርጫ አስቀድሞ መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ያሰፋል የሚለውን ተሰፋ በሙሉ አጥፍቶታል።” ብለዋል።

ሂውማን ራይትስ ወች 25ተኛ ዕትም በሆነው ባለ------ ገጹ ሪፖርት ከ90 በላይ በሆኑ ሃገራት ውስጥ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ዳስሷል፡፡ ዋና ዳይሬክተር ኬኔትዝ ሮዥ በመክፈቻ ጽሁፋቸው በችግር ወቅት ሰብዓዊ መብት ጥበቃን ማስቀደም ውጤታማ የስነምግባር መመሪያ መሆኑን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የበለጠ የደህንነት ችግርን የበለጠ እንደሚያባብስ መንግስታት አምነው እንዲቀበሉ አሳስበዋል፡፡  መሰረታዊ የነጻነት እና ያለመገለል መብት እሴቶችን በማንኳሰስ (በመጣስ) የሚገኘው የአጭር ጊዜ ጥቅም በረዥም ጊዜ የሚያስከፍለው ዋጋ አንጻር ፋይዳ የለውም፡፡ 

በ2014 ዓ.ም. እጅግ ደካማ በሆነው የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ላይ ከለጋሽ ሀገራት የተሰነዘረ ትርጉም ያለው ትችት አልነበረም። ዓመቱን በሙሉ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎችና ደጋፊዎች ላይ ጥቃት እና እስር ፈጽመዋል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በሚያዚያ እና ግንቦት ወሮች የተከሰተውን ተቃውሞ ተከትሎ የፀጥታ ሃይሎች ከተገቢው በላይ ሃይል በመጠቀም ከሃያ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የገደሉ ሲሆን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችንም አስረዋል። የመንግስት ሃይሎች ሰማያዊ ፓርቲ  የተቃውሞ ሰልፍ ለማካሄድ ያደረጋቸውን ሙከራዎች በተደጋጋሚ አግደዋል።

መገናኛ ብዙሃን በመንግስት ከፍተኛ ቁጥጥር ውስጥ እንዳሉ የቀጠሉ ሲሆን ይህም ጋዜጠኞቸ የራስ ቅድመ-ምርመራ ማድረግ አልያም ለጥቃት ፣ ለእስር ወይም ለስደት መዳረግን እንዲመርጡ አስገድዷቸዋል። በ2014 ዓ.ም. በሃያዎች የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የደረሰባቸውን ማስፈራሪያ ተከትሎ ሃገር ለቀው ተሰደዋል። በሐምሌ ወር ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁ ሰባት ጦማሪያን እና ሶስት ጋዜጠኞች ላይ መንግስት በአፋኙ የጸረ-ሽብር ህግ መሰረት ክስ መስርቶባቸዋል፡፡ በነሐሴ ወር ስድስት የግል አሳታሚዎች  ላይ በወንጀል ህጉ መሰረት ክስ የተመሰረተ ሲሆን ከክሱ ቀደም ብሎ በህትመቶቻቸው ላይ ማጥላላት እና ማስፈራሪያ ሲሰነዘርባቸው ቆይቷል። መንግስት ድረገጾችን እና ጦማሮችን ያግዳል እንዲሁም የስልክ ልውውጦችን በየጊዜው እየተከታተለ ይቀርጻል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች፡፡

የመንግስት ሃይሎች ለስኳር ልማት ተከላ ማስፋፊያ በሚል ምክንያት ያለበቂ ምክክር እና ካሳ በታችኛው ኦሞ ሸለቆ የሚገኙ ነባር ነዋሪዎችን አፈናቅለዋል።የልማት ዕቅዱ ላይ ጥያቄ ያነሱ ነዋሪዎች እና ተሟጋቾች ለጥቃት እና እስር ተዳርገዋል፡፡

የፀረ-ሽብር አዋጅ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማሕበራት አዋጅ መሰረታዊ መብቶችን ይጥሳሉ የሚሉ ውግዘቶች በጨመሩበት ጊዜ እንኳ መንግስት አዋጆቹን ለማሻሻል ምንም ፍላጎት አላሳየም። ባለስልጣናቱ በሰብዓዊ መብቶች፣ በመልካም አስተዳደር፣ በግጭት አፈታት እና በሴቶች፣ በህፃናት እና የአካል ጉዳተኛ ሰዎች መብቶች ላይ የአድቮኬሲ ስራ የሚያከናውኑ ድርጅቶች ከገቢያቸው ከ10 በመቶ በላይ ከውጭ ምንጮች መቀበል እንደማይፈቀድላቸው የሚደነግገውን የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት አዋጅ በ2014ም  ተጠናክሮ ሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል። 

“መንግስት በ2014 ዓ.ም ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን ለማፈን የወሰደው እርምጃ በ2015 ዓ.ም. ለሚደረገው ምርጫ መጥፎ ምልክት ነው”። ብለዋል ሌስሊ ሌፍኮው

Your tax deductible gift can help stop human rights violations and save lives around the world.

Region / Country