Skip to main content

ኢትዮጵያ፡ ተቃዎሞዎች ላይ የሚደረገው አፈና አልቀነሰም፡፡

ተቃዎሞ አድራጊዎች ላይ የሚፈጸመmው ግድያ እና እስር ለተከታታይ አራተኛ ወር ቀጥሏል፡፡

(ናይሮቢ፤.) – ከኖቬምበር ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል በስፋት እየተካሄደ ያለውን ሰላማዊ ተቃውሞ የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይል በጉልበት እያፈነው እንደሚገኝ ሂውማን ራይትስ ወች ዛሬ አስታወቀ፡፡ ከ2016 ዓ.ም.  መነሻ ጀምሮ በእየለቱ ሰዎች እንደሚገደሉ እና በዘፈቀደ እንደሚታሰሩ ሂውማን ራይትስ ወች አስታውቋል፡፡

የወታደራዊ ሰራዊትን ያካተተው የጸጥታ ሃይል ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ላይ የሚገኙ በርካታ ሰዎችን ቀጥታ በመተኮስ ገድሏል፡፡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረው ያለምንም ክስ እንደታገቱ ይገኛሉ፡፡ ባለፉት ሳምንታት የተቃውሞው ድግግሞሽ የቀነሰ መስሎ ቢታይም አፈናው ግን ቀጥሏል፡፡

“ኦሮሚያን በበርካታ የጸጥታ ሃይሎች የማጥለቅለቅ እርምጃ የሚያመለክተው በተማሪዎች፣ ገበሬዎች እና ሌሎች ተቃዋሚዎች የሚደረገውን ሰላማዊ ተቃውሞ ባለስልጣን አካላቱ በከፍተኛ ሁኔታ አለመፈለጋቸውን ነው::” ብለዋል በሂውማን ራይትስ ወች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌዝሊ ሌፍኮው፡፡ “መንግስት የፀጥታ ሃይሉን ሰብስቦ መመለስ ይኖርበታል፤ በስህተት የታገቱ ማንኛወንም ሰዎች መልቀቅ አለበት፤ አንዲሁም አላስፈላጊ ሃይል የተጠቀሙ የፖሊስ እና የወታደራዊ ሃይል አባላትን ተጠያቂ ማድረግ አለበት፡፡”

Protesters in Oromia region, Ethiopia, December 2015.

በጃንዋሪ 12 ቀን የአዲስ አበባ የተቀናጀ ልማት ማስተር ፕላን መሰረዙን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ያለው ሁኔታ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውቋል፡፡ የዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ማዘጋጃ ቤት ድንበር በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወደሚገኙ የእርሻ ቦታዎች ለማስፋፋት ታቅዶ በነበረው አወዛጋቢ ማስተር ፕላን ምክንያት ሰላማዊ ሰልፎች ተቀስቅሰዋል፡፡

ሆኖም የእቅዱ መሰረዝ ተቃውሞውን አልገደበውም፤ አፈናውም በመላ ኦሮሚያ ቀጥሏል፡፡ በጃንዋሪ ማገባደጃ 2016 ዓ.ም. ሂውማን ራይትስ ወች ወደ 60 የሚጠጉ ከዲሴምበር እስከ ጃንዋሪ ባለው ጊዜ የነበሩ ተቃዋሚዎችን እና ሌሎች ምስክሮችን ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ቃለ-መጠይቅ አድርኋል፤ በተቃውሞው ወቅት ከጃንዋሪ አጋማሽ ጀምሮ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መኖሩን ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ግለሰቦች ገልጸዋል፡፡ ተጠያቂዎቹ እንደገለጹት የፀጥታ ሃይሉ በተሰበሰቡ ሰዎች ላይ በዘፈቀደ በቀጥታ ይተኩሳል፣ በተቃውሞ ላይ ያሉ ሰዎችን ገድሏል፣ በርካቶችን አፍኖ ይዟል እንዲሁም ያገታቸው ሰዎች ላይ ከፍተኛ ማሰቃየት ፈጽሟል፡፡

የተወሰኑ በውጭ ባለሃብቶች የተያዙ የእርሻ መሬቶችን ማውደም እና የመንግስት መስሪያቤቶችን መዝረፍ ጨምሮ በተወሰነ መልኩ አመጻ የተቀላቀለባቸው ተቃውሞዎች እንዳሉ የሚያመላክቱ ዘገባዎች ቢኖሩም ከኞቬምበር ጀምሮ የተካሄዱት አብዛኞቹ ተቃውሞዎች ሰላማዊ ነበሩ፡፡ በፌብሯሪ 12 ቀን የፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች ከሰርግ በመመለስ ላይ ባለ አውቶብስ ተኩስ በመክፈታቸው እና ሰዎችን በመግደላቸው ሳቢያ ተቃውሞዎች እንዲነሱ እና እንዲቀጥሉ አድርጓል፡፡ መንግስት እንዳስታወቀው በፌብሯሪ 15 ቀን በፌዴራል የጸጥታ ሃይሎች እና ፖሊስ አልያም ሚሊሻ እንደሆኑ በተገመቱ የታጠቁ ሰዎች መካከል በተደረገ ግጭት ለሰባት የጸጥታ ሃይሎች ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡

Women mourn during the funeral ceremony of a primary school teacher who family members said was shot dead by military forces during protests in Oromia, Ethiopia in December 2015. December 17, 2015. © 2015 Reuters

በጃንዋሪ 10 ቀን ጸጥታ ሃይሎች በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኘው የጅማ ዩኒቨርሲቲ ቦምብ በመወርወራቸው ምክንያት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች መጎዳታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል፡፡ የተለያዩ የአይን እማኞች ለሂውማን ራይትስ ወች እንደገለጹት በጃንዋሪ 10 እና 11 ቀናት የጸጥታ ሃይሎች የጅማ ዩኒቨርሲቲን የተማሪዎች ማደሪያ ቤቶች በማጥለቅለቅ በርካታ የኦሮሞ ተማሪዎችን ለእስር እና ለድብደባ ዳርገዋቸዋል፡፡

የጸጥታ ሃይሎች ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ የመንግስት ባለስልጣናትን፣ ነጋዴዎችን፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን፣ የጤና ባለሙያዎችን፣ እንዲሁም ለሚያመልጡ ተማሪዎች እርዳታ የሚያደርጉ እና መጠለያ የሚሰጡ ሰዎችን አስረዋል፡፡ በኦሮሚያ የሚገኙ የአንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከመጀመሪያዎቹ ተቃዋሚዎች መካከል ስለሆኑ በእብዛኞቹ የታሰሩት ከ18 ዓመት እድሜ በታች የሆኑ ህጻናት ናቸው፡፡

“ቀጥታ ወደ ግቢው በመግባት ባነጣጠሩት ጥቁር መሳሪያ ሶስት ተማሪዎችን ተኩሰው መተዋል” ብሏል አንድ የ17 ዓመት ተማሪ ማስተር ፕላኑን በመቃዎም በተደረገው ሰልፍ የጸጥታ ሃይሎችን እርምጃ ሲያስረዳ “ፊታቸው ላይ ነው ተመተው የነበሩ ስለሆነ ተገድለዋል፡፡”

ሂውማን ራይትስ ወች የተቃውሞ ሰልፉ ከተጀመረበት ከኖቬምበር 12 ቀን ጀምሮ ታግተው የነበሩ 20 ሰዎችን አናግሯል፤ ሁሉም ፍርድ ቤት አልቀረቡም፡፡ አስራ አራቱ ሰዎች በታገቱበት ወቅት እንደተደበደቡ ገልጸዋል፤ አንድ አንዴ ድብደባው የከፋ እንደነበረም አስታውቀዋል፡፡ በርካታ ተማሪዎች በወገባቸው ተንጠልጥለው ታስረው እንደነበር እና እንደተገረፉ አስታውቀዋል፡፡ አንድ የ18 ዓመት ተማሪ እግሩን በኤሌክትሪክ እንደነዘሩት ተናግሯል፡፡ ሁሉም ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ተማሪዎች ሌሎች ተማሪዎች ተቃውሞውን እንዲቀላቀሉ ቀስቅሳችኋል በሚል በባለስልጣን አካላቱ ተወንጅለዋል፡፡ በርካታ ታግተው የነበሩ ሴት ተማሪዎች በፀጥታ ሃይሎቹ ፆታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል አሊያም ያልተገባ አያያዝ ተፈጽሞባቸዋል፡፡

የተገለጸው አያያዝ ሂውማን ራይትስ ወች እና ሌሎች የመብት ተሟጋች ቡድኖች በኦሮሚያ በግልጽ በሚታወቁ እና ድብቅ በሆኑ እስር ቤቶች እስረኞች ላይ የሚፈጸሙ የማሰቃየት እና ያልተገባ አያያዝ መንገዶችን ያሟላሉ፡፡ በርካታ የአይን እማኞች እና የቀድሞ ታሳሪዎች እንደገለጹት በምዕራብ ሸዋ እና ቦረና ዞኖች የጸጥታ ሃይሎች የንግድ ተቋማት እና የመንግስት ህንጻዎችን እንደ ጊዜያዊ የማገቻ ቦታነት ይጠቀሙባቸዋል፡፡

ይህ በሚጻፍበት ወቅት በኦሮሚያ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች እንደተዘጉ ያሉ ሲሆን ይኼውም ባለስልጣን አካላት ተጨማሪ ተቃውሞዎችን ለስማቆም ሲሉ መምህራንን ስላሰሩ እና መገልገያ ቁሳቁሶችን ስለዘጉ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተማሪዎች እንደ አንዱ የተቃውሞ መግለጫ ትምህርት መከታተል ስላቆሙ ወይንም እስርን በመፍራታቸው ነው፡፡ በርካታ ተማሪዎች በቅድመ ሁኔታ ከታገቱበት የተለቀቁ ሲሆን ቅድመ-ሁኔታውም ህዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ ከአንድ ሰው በላይ ሌላ ተጨማሪ ሰው ጋር ላለመታየት ቃል መግባታቸው ነው፤ አንዲሁም በርካቶቹ ይህን ቅድመ-ሁኔታ ለመቀበላቸው ምክንያት እንደሆነ ለማሳያነት እንዲፈርሙ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

Security forces harassing students in Oromia, January 2016.  © 2016 Private

ሂውማን ራይትስ ወች አጠቃላይ የተገደሉ ሰዎችን ቁጥር ለማረጋገጥ አልቻለም ምክንያቱም በኢትዮጵያ ያለው እንቅስቃሴ እና በነጻነት የመዘገብ ሁናቴ የተገደበ በመሆኑ ነው፡፡ ተሟጋቾች በተለይ ከማህበራዊ ድረ-ገፆችን መሰረት በማድረግ ባገኟቸው የቪዲዮ፣ የፎቶ እና የድረ-ገጽ ላይ ጽሁፎች መረጃዎች መሰረት ከኖቬምበር 12 ቀን ጀምሮ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ያለው መረጃ እንሚጠቁመው በበርካታ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ታስረዋል፤ በርካቶቹ የት እንሚገኙም አይታወቀም፤ የሚገመተው በሃይል እንዲሰወሩ መደረጉን ነው፡፡

ሂውማን ራይትስ ወች ከዚህ በፊት ተገልጾ ያልነበረ የ12 ሰዎችን ግድያ መዝግቧል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የአብዛኞቹ ግድያ የተፈጸመው በደቡባዊ ኦሮሚያ የሚገኙት የአርሲ እና ቦረና ዞኖች ሲሆን እነዚህ ቦታዎች ተቃውሞዎች ሲካሄዱባቸው የነበሩ ቦታዎች ቢሆንም ከሌሎች አካባቢዎች አንጻር ዝቅተኛ ትኩረት የተሰጣቸው ቦታዎች ናቸው፡፡ “ይህ ሚያሳየው በአጠቃላይ በኦሮሚያ ያለው የተቃውሞ እና የሚፈጸም ጥቃት መጠን ከተዘገበው በላይ ሊሆን እንደሚችል ነው” ብሏል ሂውማን ራይትስ ወች፡፡

የኢትዮጵያ መንግስት በገለልተኛ የሲቪክ ማህበረሰብ ቡድኖች ላይ እና መገናኛ ብዙሃን ላይ በሚፈጽመው ወደር-አልባ እገዳ ምክንያት ከተጠቁት አካባቢዎች የሚገኘውን መረጃ እጅግ አነስተኛ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ነገር ግን ማሕበራዊ ድረ-ገጾች የተቃውሞ ሰልፎችን ፎቶ እና ቪዲዮ ባካተተ መልኩ በተለይ በኖቬምበር እና ዲሰምበር አሰራጭተዋል፡፡

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ(ኦኤምኤን) በተቃውሞው ወቅት መረጃ በመላው ኦሮሚያ እንዲሰራጭ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል፡፡ ኦ ኤም ኤን ዳያስፖራን መሰረት ያደረገ የቴሌቪዝን ጣቢያ ሲሆን መረጃዎችን በተለይ በኦሮምኛ ቋንቋ በሳተላይት የሚያስተላልፍ እና በቅርቡም በአጭር ሞገድ የሬድዮ ፕሮግራም የጀመረ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት የዓለም አቀፍ ደንቦችን በሚጥስ መልኩ ኦ ኤም ኤን ስርጭት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ለ15 ተከታታይ ጊዜያት የአየር ሞገዱን ለማገድ መሞከሩ ተዘግቧል፡፡ ሁለት ነጋዴዎች ለሂውማን ራይትስ ወች እንደገለጹት በንግድ ቦታቸው ላይ ኦ ኤም ኤንን አሳይታችኋል ተብለው ታስረው ነበር፡፡ በበርካታ አካባቢዎች ኦ ኤም ኤንን የሚያስተላልፉ የሳተላይት ዲሾንን የፌዴራል ፖሊስ አውድሟል፡፡ ተማሪዎች የተለያዩ ቪዲዮዎችን በማህበራዊ ድረ ገጾች አውጥታችኋል እንዲሁም ለኦ ኤም ኤን መረጃ ታቀብላላችሁ በሚል መወንጀላቸውን ገልጸዋል፡፡ ባለፉት ወራት በኦሮሚያ የሚደርሰውን ጥቃት በተመለከተ የሚወጣው መረጃ ጥቂት በመሆኑ ሳቢያ እስሩ እና እታሰራለሁ የሚለው ስጋት ጨምሯል፡፡

“የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሚጠቀሙትን ከመጠን ያለፈ ሃይል ማስቆም አለበት፤ በዘፈቀደ የታሰሩ ሁሉንም ሰዎች ነጻ መልቀቅ አለበት አንዲሁም ግድያውን እና ሌላ የጸጥታ ሃይሎች ጥቃትን በተመለከተ ገለልተኛ ማጣራት መደረግ ይኖርበታል” ብሏል ሂውማን ራይትስ ወች፡፡ “የከፋ የመብት ጥሰት ያደረሱ አካላት በተገቢው መንገድ ክስ ሊመሰረትባቸው ይገባል፤ ጥቃቱ የተፈጸመባቸውም ሰዎች ተገቢው ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡”

በጃንዋሪ 21 ቀን የአውሮፓ ፓርላማ አፈናውን በመቃዎም ጠንካራ አቋም አሳልፏል፡፡ ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ ግጭቱን በተመለከተ ይፋዊ ውግዘት አላቀረቡም ይልቁንም ህዝባዊ ምክክር እና ውይይት እንደሚያስፈልግ በሁለት መግለጫዎች አስታውቀዋል፡፡ በሌላ በኩል የተወሰኑ መንግስታት የኢትዮጵያ መንግስትን ተግባር በተመለከተ ቅሬታ እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡ “ሁለቱ የኢትዮጵያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ወዳጆች ዩናይትድ ኪንግደም እና ዩናይትድ ስቴትስ አመጻ ያዘለውን አፈና ለማስቆም ተጨማሪ ማድረግ የሚችሉት ነገር እንዳለ እና ጥቃቱን በተመለከተ ገለልተኛ የማጣራት ተግባር እንዲካሄድ ጥሪ ማቅርብ አለባቸው” ብሏል ሂውማን ራይትስ ወች፡፡

“የኢትዮጵያ ለጋሽ ሃገሮች ምላሽ አርኪ አይደልም ሌላው ቢቀር በኦሮሚያ ለተገደሉት በርካታ ሰላማዊ ሰልፈኞች” ብለዋል ለዝሊ ሌፍኮው “ይህን ዘግናኝ ጭካኔ ችላ ማለትም ሆነ አቃሎ ማየት ማቆም ይኖርባቸዋል እንዲሁም በግድያው እና በተፈጸመው ጥቃት ዙሪያ መንግስት ገለልተኛ የማጣራት ተግባር እንዲካሄድ እንዲደግፍ ጥሪ ማቅረብ አለባቸው፡፡”

ለተጨማሪ መረጃ እና በተጠቂዎች ላይ ስለቀረበው የአይን እማኞች ማስረጃ እባክዎ የታችኛውን ይመልከቱ

በኦሮሚያ የተማሪዎች ተቃውሞ የተጀመረው በኖቬምበር 12 ቀን 2015 ዓ.ም ጊንጪ በመባል በምትታወቀው ከኢትዮጵያ ዋና ከተማ አዲስ አበባ በስተ ደቡብ ምዕራብ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው አነስተኛ ከተማ ሲሆን መንስዔውም የመንግስት ባለስልጣን አካላት በአካባቢው የሚገኘውን ደን ለኢንቨስትመንት ልማት በሚል ለመመንጠር በመሞከራቸው ነው፡፡ ተቃውሞው ወዲያው ወደ ሌሎች የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተስፋፋ ሲሆን የተቃውሞው ጥያቄም በመስፋት የአዲስ አበባ የተቀናጀ የልማት ማስተር ፕላን በመባል የሚታወቀውን የአዲስ አበባ ማዘጋጃቤት ድንበር የማስፋፋት እቅድ ተቃውሞ ያካተተ ሆኗል፡፡ ተቃውሞው እስከ ዲሰምበር ወር ሲቀጥል ገበሬዎች እና ሌሎችም ተቃውሞውን ተቀላቅለዋል፡፡

በርካታ ተቃውሞ አድራጊዎች እንዳስታወቁት መንግስት ተቃውሞውን በጉልበት ለማስቆም የፈጸመው ተግባር እና በዚህም ምክንያት እየጨመረ የሄደው የሟቾች ቁጥር የተቃውሞውን ትኩረት ተቃውሞ አድራጊዎች ላይ ስለሚፈጸመው ግድያ እና እስር እንዲሁም ለበርካታ አስርት ዓመታት በተፈጸመው ታሪካዊ የኦሮሞ ብሶት ላይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ኦሮሚያ ለበርካታ ኢትዮጵያዊያን መኖሪያ ናት፤ 35 ሚሊየን ለሚገመቱ ኦሮሞች አሉ ይኼውም የሃገሪቱ ከፍተኛ መጠን ያለው የጎሳ ቡድን ነው፡፡ በርካታ ኦሮሞች በተከታታይ ጊዜ በነበሩ የኢትዮጵያ መንግስታት መገለል እና መድሎ እንደደረሰባቸው ይሰማቸዋል፡፡ ተቃውሞ የሚያሰማ የኦሮሞ ጎሳ አባል ብዙውን ጊዜ ለእስር እና ለስቃይ ይዳረጋል አሊያም በእስር ላይ ያልተገባ አያያዝ ይፈጸምበታል፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል ተብሎ ይወነጀላል፤ ግንባሩ በመንግስት ላይ በተውሰነ መልኩ የትጥቅ ትግል የሚያካሂድ እና በሃገሪቱ ፓርላማ አሸባሪ ተብሎ የተመደበ ድርጅት ነው፡፡

በዲሴምበር 16 ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ “መንግስት አካባቢውን ለማበጣበጥ ለሚሞክር ማንኛውም ሃይል ላይ ምህረት የለሽ ህጋዊ እርምጃ” እንደሚወስዱ አስታወቁ፡፡ በተመሰሳሳይ ቀን የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳሉት “ቀውስ እና ብጥብጥ ለመፍጠር ያለመ የተደራጀ እና የታጠቀ የአሸባሪ ቡድን ሞዴል አርሶ አደሮችን፣ የህዝብ አመራሮችን፣ እና ሌሎች በክልሉ የሚኖሩ የሌላ ጎሳ አባላትን መግደል ጀምሯል፡፡” ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ወታደራዊ ሰራዊቱን እና የፌዴራል ፖሊሲን ያካተተ የፌዴራል የጸጥታ ሃይል በኦሮሚያ ያለውን የህግ ማስከበር ተግባር እየመራ ይገኛል፡፡

በጃንዋሪ 12 ቀን ኦሮሚያን በመወከል የገዢው ፓርቲ ግንባር አባል የሆነው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በሃገሪቱ የመንግስት ቴሌቪዥን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን እቅድ መሰረዙን አስታወቀ፡፡ ይህ ውሳኔ ያልተጠበቀ የፖሊሲ ለውጥ ቢሆንም ሂውማን ራይትስ ወች ቃለ-መጠይቅ ያደረገላቸው ሰዎች እቅዱ በእርግጥ ያለበት ሁኔታ እና መንግስት መሰረዙ እንደጸና እንዲቆይ ስለማድረጉ አወዛጋቢ ነገሮች አሉ ብለዋል፡፡

ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በ2014 ዓ.ም. ይፋ ሲሆን በመላ ኦሮሚያ ተቃውሞዎች ተነስተው ነበር፣ ይኼንን ተቃውሞ የጸጥታ ሃይሎች በተኩስ በትነውታል፤ በትንሹ በርካታ በደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎችም ተገድለዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ታስረዋል፡፡ ከታሰሩት ውስጥ በርካታዎቹ ክስ ሳይመሰረትባቸው እንደታገቱ ቆይተዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም. ተደርጎ በነበረው ተቃውሞ ታስረው ከነበሩ ሰዎች መካከል ሂውማን ራይትስ ወች ካናገራቸው 25 ያህል ሰዎች በርካታዎቹ በእስር ላይ እንዳሉ የማሰቃየት ተግባር እና ያልተገባ አያያዝ ተፈጽሞባቸዋል፡፡ ቀድሞ ታስረው የነበሩ በርካታ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርቲዎች እንዲመለሱ አልተፈቀደላቸውም፡፡ በዲሰምበር 2 ቀን 2015 ዓ.ም. አምስት የኦሮሞ ተማሪዎች በ2014 ዓ.ም. በነበረው ተቃውሞ በነበራቸው ሚና ምክንያት የጸረ-ሽብር ህጉን በመጣስ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ በ2014 ዓ.ም. በነበረው ተቃውሞ ያልተመጣጠነ እና እስከ መግደል የሚያደርስ ሃይል ስለመጠቀሙ በመንግስት  ምንም አይነት የማጣራት ተግባር አላከናወነም፡፡

ማጠቃለያ ግድያዎች፣ አላስፈላጊ እስከ መግደል የሚያደርስ ሃይል አጠቃቀም

በ2015 ዓ.ም. የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት በነበሩ ተቃውሞዎች የተቃውሞ ሰልፉን ለመበተን ምላሽ የሰጡት በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል ፖሊሶች ናቸው፣ እነሱም በተቃዋሚዎቹ ላይ አስለቃሽ ጭስ ተጠቅመዋል በአንድ አንድ አጋጣሚዎችም ቀጥታ ወደተቃውሞ አድራጊዎቹ የተኮሱበት ጊዜ አለ፡፡ በመጀመሪያ ላይ አብዛኛዎቹ ግድያዎች እንደተፈጸሙ የተመዘገበው በምሽት ሲሆን ይኼውም የጸጥታ ሃይሎች ቤት ለቤት ተቃውሞ አድራጊዎቹን በማደናቸው ነው፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎችን ለማምለጥ ሲሞክሩ የገደሏቸው ሲሆን የተቀሩትን በሚታሰሩበት ወቅት በተነሳ አምባጓሮ ነው የተገደሉት ሆኖም የበርካቶቹ ሞት ትክክለኛ ምክንያት አልታወቀም፡፡

በዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መስፈርት መሰረት የህግ አስከባሪ አካል እስከ መግደል የሚያደርስ ሃይል መጠቀም ያለበት ራስን ለመከላከል ወይንም በሌሎች ሰዎች የህይወት ላይ አደጋ የሚያመጣ ከሆነ ነው፡፡

የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በዲሴምበር 16 ቀን “መንግስት አካባቢውን ለመበጥበጥ የሚሞክሩ ማንኛውም ሃይሎች ላይ ምህረት የለሽ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል” ካሉ በኋላ የአይን እማኞች እንደገለጹት የፌዴራል ፖሊስ እና ወታደራዊ ሰራዊት ከኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጋር በጋራ እንዲሰሩ በመላ ኦሮሚያ ተሰማሩ፡፡ በርካታ ታቃውሞ አድራጊዎች እንደገለጹት የፌዴራል ፖሊስ እና ወታደሮች ቀጥታ የተቃውሞ ሰልፍ የሚያደርጉ ሰዎች ላይ ተኩሰዋል፡፡

ከምዕራብ ሸዋ የ17 ዓመቱ የተቃውሞ አድራጊ ዋቆ- ስሙ እንደሌሎቹ ሁሉ ለደህንነቱ ሲባል የተቀየረ ለውጡን እንደሚከተለው አብራርቶታ፤

በተቃውሞው የመጀመሪያ ወቅቶች (በኖቬምበር አጋማሽ) የኦሮሚያ ፖሊስ ወደየቤታችን እንድንመለስ ሊመክረን ሞክሯል፡፡ ተቃወምናቸው ስለዚህ በአስለቃሽ ጋዝ ሰልፉን በተኑት አና በርካቶችን አሰሩ፡፡ ከበርካታ ቀናት በኋላ ሌላ ተቃውሞ አደረግን፡፡ በዚህ ወቅት እነሱ (የፌዴራል ፖሊስ) መጡ፡፡ በርካታ ጥይቶችን ወደ ሰማይ ተኮሱ፡፡ ህዝቡ ሊበተን ስላልቻለ አስለቃሽ ጭስ ተኮሱ እናም በዚህ ግር ግር ላይ እያለን የጥይት ድምጾችን መስማት ጀመርን ከእኔ ጎን የነበሩ ተማሪዎችም ባሉበት መውደቅ ጀመሩ፡፡ ጓደኛየ (ስሙ ያልተጠቀሰ) በጥይት ተመቶ ተገደለ፡፡ እሱን ለመግደል ኢላማ ተደርጎ አልነበረም፤ ወደ ተሰበሰበው ህዝብ ቀጥታ በዘፈቀደ ነበር የሚተኩሱት፡፡

ከአርሲ ነገሌ የ16 ዓመት እና የ10ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ጉዲና ደግሞ በዲሰምበር መጀምሪያ አካባቢ በነበረው ተቃውሞ የባለስልጣን አካላቱን ምላሽ እንደሚከተው አብራርቷል፤

ሁሉም ትምህርት ቤቶች በአንድ ላይ ሆነው በህብረት ወደ አደባባይ ወጡ፡፡ ተቃውሞ እያደረግን ባለንበት ወቅት አስለቃሽ ጭሶች ተወረወሩ፣ እኛ ጉዟችንን ቀጠልን ከዚያም ከኋላችን የጥይት ተኩስ ሰማን፤ በርካታ ተማሪዎች ተመተው የስቃይ ድምጽ እያሰሙ ወደቁ፡፡ አንድ በጣም ወጣት የእኔ ትምህርት ቤት ልጅ ጉሮሮው ላይ ተመቶ ደም በብዛት ሲፈስ አይቻለሁ፡፡ ሁልጊዜ ማታ ይህ ተማሪ በህልሜ ይመጣብኛ፡፡

በተለይ ከዲሴምበር አጋማሽ ጀምሮ በዋናነት የፌዴራል ፖሊስን ያካተተው የጸጥታ ሃይል ወደተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹ ቀጥታ መተኮሱን በማስመልከት በአርሲ፣ ምዕራብ ሸዋ እና ምስራቅ ወለጋ ዞኖች የነበሩ ተቃውሞ አድራጊዎች ተመሳሳይ ክስተቶችን አስረድተዋል፡፡ አስለቃሽ ጭስ ሲጠቀሙ እና ቀጥታ ወደ ህዝቡ ጥይት ሲተኩሱ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ አሊያም ያለበቂ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ነው፡፡

በተለያየ ጊዜ ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ሶስት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከአርሲ አንድን ክስተት እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፡ የ17 ዓመቱ ኩማ እንዳለው፤

የስድሰተኛ ክፍል ተማሪ እንደተገደለ ሰማን (በጎረቤታማ መንደር)፡፡ ወንድማማችነታችንን ለማሳየት ስንል ተቃውሞ ለማድረግ ወሰንን፡፡ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች በጋራ ተሰባስበን ወደ መንግስት መስሪያ ቤቶች መዝመት ስንጀምር የጸጥታ ሃይሎች ወደ እኛ መምጣት ጀመሩ፡፡ አስለቃሽ ጭስ ወረወሩ ከዚያም የጥይት ተኩስ ድምጽ ሰማን፡፡ ጓደኛዬ (ስሙ ያልተገለጸ) ደረቱ ላይ ተመታ፡፡ እየደማ ሲወድቅ አይቸዋለሁ፡፡ እየሮጥን ተመለስን ወደኋላ ዞሬ አላየሁም፡፡ እናቱ በኋላ ጓደኛዬ እንደተገደለ ነገረችኝ፡፡ 17 ዓመቱ ነበር፡፡

ተቃውሞ የማድረግ መታቀዱን ተከትሉ ለመሳተፍ ያላቸውን ተስፋ ለማጨናገፍ የጸጥታ ሃይሎች በሻሸመኔ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስት ገብተዋል፡፡ የ9ነኛ ክፍል ተማሪ የሆነው የ17 ዓመቱ ገመዳ የሚከተለውን ብሏል፤

ተቃውሞ ለማድረግ እቅድ ነበረን፡፡ በጧት 2 ሰዓት የኦሮሚያ ፖሊስ በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ መጣ፡፡ አራት ተማሪዎችን አሰሩ (ከ9-11ኛ ክፍል) የቀረነው ሌሎቻቸን ነገሩ ስላበሳጨን ፖሊሶቹ ላይ መጮህ ጀመርን፡፡ አንዱ ፖሊሶቹ ላይ ዲንጋይ ወረወረ አናም ፖሊሶቹ በፍጥነት ከግቢው ወተው በመሄድ ከአንድ ሰዓት በኋላ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ተመልሰው መጡ፡፡ቀጥታ ውደ ግቢው በመግባት ሶስት ተማሪዎችን በጥቁር ጠመንጃ ተኩሰው ገደሉ፡፡ ፊታቸው ላይ ነበር የተመቱት እና ተገድለዋል፡፡ አስከሬናቸውን ይዘው ሄዱ፡፡ ጧቱን ሙሉ በየክፍላችን እንድንቆይ አደረጉን እና ቀትር ላይ ተመልሰው በመምጣት እኔን ጨምሮ 20 የምንሆን ተማሪዎችን ወሰዱን፡፡

ዘፈቀዳዊ እስር እና እገታ

በበርካታ ደርዘኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሂውማን ራይትስ ወች እንደተናገሩት ያለ በቂ መሰረት ጓደኞቻቸው አሊያም የስራ አጋሮቻቸው ታስረዋል፤ በርካታዎቹ ታሳሪዎች የገቡበት ቦታ አልታወቀም፡፡ ከተለያዩ ኦሮሚያ አካባቢዎች የተውጣጡ አስራአምስት ተቃውሞ አድራጊዎች በራሳቸው ላይ የደረሰውን እስር አብራርተዋል፡፡ በቀን ከተከናወነ የተቃውሞ ሰልፍ በኋላ ሁልጊዜ በምሽት የጸጥታ ሃይሎች ቤት ለቤት በመዘዋወር በተቃውሞ ሰልፉ ታሳትፎ ያላደረጉ ተማሪዎችን ጭምር የሚያስሩ ሲሆን በጃንዋሪ 9 ቀን በቦረና ዞን አንድ የ 8 ዓመት ታዳጊ ጭምር አስረዋል፡፡ የመጀመርያ አላማቸው አዋቂ እና ወጣት ወንዶችን ነው ሆኖም በርካታ ሴቶች እና ልጃገረዶችም ጭምር ታስረዋል፡፡ የተያዙ ሰዎች ወደ ፖሊስ ጣቢያ፣ ወታደራዎ ካምፕ እና ጊዜያዊ የማቆያ ማዕከል ይወሰዳሉ፡፡

ከቦረና ዞን የ7ተኛ ክፈሉ ኩማ በዲሴምበር ወር መጀመሪያ አካባቢ ታስሮ ነበር፤ ባልታወቀ ስፍራ ለአምስት ቀናት ተይዞ የቆየ ሲሆን በእንጨት ብትር ተደብድቧል፡፡

“ለምን የተቃውሞ ሰልፉ ውስጥ ገባህ? መንግስትን ትጠላለህ ማለት ነው? ለምን? መልካም ነገር አላደረግንልህም?” ብለው ጠይቀውኛል፡፡ ከዚያም ከኦነግ (መንግስት በአሸባሪ ቡድንነት የፈረጀው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር) ጋር ግንኙነት እንዳለኝ መናገር ጀመሩ፡፡ የተቃውሞ ሰልፉ ከኦነግ ጋር ምን የሚያገናኘው ነገር እንዳለ ጠየቁኝ፡፡ ከአንድ ሰው በላይ ተጨማሪ ሰው ጋር ህዝብ ወደሚሰበሰበበት ቦታ እንደማልሄድ ቃል የገባሁበትን ወረቀት ካስፈረሙኝ በኋላ ለቀቁኝ፡፡ ከበርካታ ቀናት በኋላ ሌላ ተቃውሞ ነበረ፤ በዚህኛው ተቃውሞ አልተሳተፍኩም ሆኖም ልታሰር እንደምችል አውቅ ነበር፡፡ የተኩስ ድምጾችን እየሰማሁ ቤት ቁጭ ብየ ዋልኩ ሙሉ ቀን፤ የሚገደሉት ሰዎች የማላውቃቸው እንዲሆኑ ተስፋ እያደረኩ ነበር፡፡

የ7ተኛ ክፍሉ ተማሪ ገመዳ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ በታቀደበት ቀን በትምህርትቤቱ ግቤ እያለ ታስሮ እንደነበር ተናግሯል፡

ለ10 ቀናት በፖሊስ ጣቢያ ተይዤ ቆይቻለሁ፡፡ ለመጀመሪያዎቸሁ ሶስት ቀናት ሁልጊዜ ማታ ማታ በእንጨት በትር ጀርባየን እና እግሬን ይደበድቡኝ ነበር፣ እንዲሁም ከተቃውሞው ጀርባ ማን እንዳለ እና የኦነግ አባል እንደሆንኩ ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ከተፈታሁ ከበርካታ ሳምንታት በኋላ ተቃውሞ በከተማዋ እንደገና ተጀመረ፡፡ ደግመው አሰሩኝ፡፡ ተመሳሳይ ድብደባ እና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ቤተሰቤ ለፖሊስ ጉቦ በመክፈል እንድፈታ አደረጉኝ፡፡

የባለስልጣን አካላቱ የተቃውሞ ሰልፍ አድራጊዎቹን እንደረዱ የተገለጹ ሰዎች ላይ የጋራ ቅጣት ጥለዋል፡፡ በዲሴምበር መጀመሪያዎቹ አዳባቢ በአርሲ ከጸጥታ ሃይሎች ያመልጡ የነበሩ ተቃውሞ አድራጊ ተማሪዎችን እንደረዳች የታወቀባት ሌሊሳ እንዳለችው፡

ተቃውሞውን አልተቀላቀለኩም ሆኖም የተኩስ ድምጽ ሙሉ ቀን እና ማታም ጭምር እሰማ ነበር፡፡ ተማሪዎች ወደአገኙት ቦታ እየሮጡ ራሳቸውን ለመደበቅ ይሞክሩ ነበር፡፡ አስር ተማሪዎች ወደ እኔ መጡ እና እንድደብቃቸው እርዳታን ስለጠየቁ ከፖሊስ እንዲደበቁ አደረኩ፡፡ ፖሊስ በምሽት ከቤት ለቤት በመንቀሳቀስ ተማሪዎችን ያስር ነበር፡፡ ወደቤቴ መጡ እና ሁሉንም ወንዶች አሰሯቸው እኔም የቀሩት ሶስቱ ሴቶች ልጆቼ መሆናቸውን አሳመንኳቸው፡፡ከዚያም ከአንድ ሰዓት በኋላ ተመልሰው መጥተው ባለቤቴን አሰሩት፡፡ እኔ ፊት ደብድበውታል፣ እንዳይገድሉት ስለምናቸው እኔን በያዙት ጠመንጃ በሰደፍ መቱኝ፡፡ ባለቤቴን ይዘውት ሄዱ፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስለእርሱ የሰማሁት ነገር የለም፡፡

የግል ትምህርት ቤት ባለቤት የሆነው ነጋሱ የእርሱ ትምህርትቤት ተማሪዎች በተቃውሞው ስለተሳተፉ መታሰሩን አመልክቷል፡

የግል ትምህርት ቤት አለኝ (ቦታው ያልተጠቀሰ)፡፡ ተማሪዎቹ አመጹ ሆኖም ፖሊስ ሰልፉን በጉልበት አልበተነውም ይልቁንስ በፊልም ሲቀርጹ ቆይተው ማታ ላይ ብዙ ሰዎችን አሰሩ፡፡ ከታሰሩት ውስጥ አራቱ ተቃውሞ አድራጊዎች ከኔ ትምህርት ቤት ነው፡፡ ስለዚህ ፖሊስ በማታ ቤቴ መጥቶ አሰረኝ እኔንም እና ወደ ጦር ካምፕ ወሰዱኝ (ስሙ ያልተገለጸ)፡፡ ለአምስት ቀናት ያህል ብቻዬን አንድ ጨለማ ጉድጓድ ውስጥ ተይዤ ቆየሁ፡፡ በጣም ቀዝቃዛ ነበር ለሁለት ቀናትም ምንም አይነት ምግብ አልሰጡኝም፡፡ ማታ ማታ ይደበድቡኝ ነበር እንዲሁም የኦሮሞ ፌዴራሊስት ንቅናቄ እና ኦነግ ለተባሉት የተቃዋሚ ቡድኖች የገንዘብ እርዳታ እንደሰጠሁ ይወንጅሉኝ ነበር፡፡ እንዲሁም በማህበራዊ ድረ-ገጽ ቪድዮዎችን ለጥፈሃል እና ለኦ ኤም ኤን ልከሃል ብለው ወንጅለውኛል፡፡ ዝምብለው ነበር ይኄን የሚሉት፡፡ ትምህርትቤቴን እንዲዘጋ ካደረጉ በኋላ የባንክ አካውንቴን እንዳይንቀሳቀስ አደረጉት፡፡ ቤቴንም ወስደውብኛል፡፡ አሁን ምንም የለኝም ተማሪዎቹም እኔ በማቆያ ቦታዎች  ያለፍኩበትን መንገድ እያለፉበት ነው  አሊያም ትምርት ቤቶቹ ስለተዘጉ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አልቻሉም፡፡

ተናጋሪ እንደሆኑ የሚታወቁ ተማሪዎች እና ከቤተሰባቸው አባላት ውስጥ የተቃውሞ ፖለቲካ ታሪክ እንዳላቸው የሚታወቁ ተማሪዎች የበለጠ አደጋ ላይ ናቸው፡፡ የ25 ዓመቱ ሌንጮ እንዳለው

በጣም ተናጋሪ እንደሁንኩ እና የተማሪዎች መሪ እንደሆንኩ እታወቃለሁ፡፡ አባቴም ቢሆን መንግስትን በመቃወም የታወቀ ነው፡፡ ስለሰጋሁ በተቃውሞ ሰልፉ እንኳን አልተሳተፍኩም ነበር ነገር ግን ተቃውሞውን እንዳስተባበርኩ ተደርጎ ተለይቻለሁ፡፡ ታስሬ ነበር እና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ስወሰድ የአካባቢው ባለስልጣናት፣ የኦሮሞ አርቲስት (ዘፋኝ) መምህሮቼን እና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ በተናጋሪነታቸው የሚታወቁ ሁሉንም ተማሪዎች አይቻቸዋለሁ፡፡ ተጽዕኖ ፈጣሪ ናቸው ብለው የገመቷቸውን በሙሉ እያሰሩ ነበር የሚገኙት፡፡ ሁሉም ስጋት ስለነበራቸው የተቃውሞ ሰልፉን ተቀላቅለው ነበር ብዬ ለመገመት ይከብደኛል፡፡

በሃገሪቱ በህግ የተመዘገበውን የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ አባላትን ጨምሮ ታዋቂ የኦሮሞ ምሁራን ጭምር ታስረው ነበር፡፡ በዲሰምበር 23 ቀን ምክትል ሊቀ መንበሩ በቀለ ገርባ ከቤቱ ተይዞ ማሰቃየት እና ያልተገባ የእስረኞች አያያዝ እንደሚጸምበት ወደሚታቀው አዲስ አበባ የሚገኘው ማዕከላዊ እስር ቤት ተወስዷል፡፡ በጃንዋሪ 22 ቀን ፍርድቤ የቀረበ ሲሆን በአፋኙ የጸረ-ሽብር ህግ መሰረት ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን በመግለጽ አቃቢ ህግ ለተጨማሪ የምርመራ ጊዜ 28 ቀናት ተሰጥቶታል፡፡ በቀለ በኦሮሚያ ፖለቲካ ውስጥ ለዘብተኛ ድምጽ ያለው ተቃዋሚ ሲሆን አመጻ አልባ ተቃውሞን በሙሉ እምነት ሚደግፍ እና የሚያበረታታ ነው፡፡

በተቃውሞው በንቃት እንደሚሳተፉ ከተገለጹት ሰዎች በተጨማሪ የፀጥታ ሃይሎች ሌሎች ተጽኖ ፈጣሪ ሰዎችንም አስረዋል፤ ከእነዚህም ወስጥ ታዋቂ የኦሮሞ ነጋዴ ሴቶች፣ መምህራን፣ ፕሮፌሰሮች፣ እና በርካታ ዘፋኞች እና አርቲስቶች ይገኙበታል፡፡ አንድ መምህር እንዳለው፡

ተማሪዎቹ ተቃውሞ አስነስተዋል፡፡ በማታ መጥተው በርካቶችን አሰሯቸው፤ የኔ ተማሪዎች ማታ ላይ ደውለውልኝ ፖሊስ ሊያስራቸው በራቸው ላይ እንደሚገኝ ገልጸውልኛል፡፡ ከዚያም በርካቶቹ መምህራንም እንደታሰሩ ሰማሁ፡፡ በዛ ምሽት ከከተማ ውጭ ነበርኩ፡፡ ከዚያም የወረዳው አስተዳዳሪ ደወለልኝ እና ላስቆማቸው ስላልቻልኩ ለተማሪዎቼ ተግባራት እኔ ተጠያቄ እንደሆንኩ ገለጸልኝ፡፡ እኔ ከመጀመሪያውም የአዲስ አበባን ማስተር ፕላን መተግበር እና አንዴት ተማሪዎቹን ይህ እቅድ ለእነሱ ጥሩ እንደሚሆን ለማሳመን በተመለከተ በሚደረግ ውይይት ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ስላለሆንኩ ቀድሞውንም ችግር ላይ ነበርኩ፡፡

አሁን በስደት ላይ የሚገኝ አንድ ታዋቂ ኦሮሞ ዘፋኝ የሚከተለውን ብሏል፡

አንድ ዘፈን በዩቲዩብ ለቀኩ (በዲሰምበር ወር) ዘፈኑም ስለተቃውሞው የሚናገር እና ተማሪዎች ዝምታውን በመስበር በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ይፋ እንዲያወጡት የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በዘፈኖቼ ምክንያት ለሶስት ጊዜያት ታሰሬ አውቃለሁ፡፡ ዘፈኖቼ የኦሮሞ ታሪክ አና ባህል ላይ ያጠነጠኑ ናቸው ሆኖም ፖለቲካዊ ይዘት እንዳላቸው እንዳይታወቁብኝ እጠነቀቅ ነበር፡፡ ሆኖም አሰሩኝ፡፡ ለስስተኛ ጊዜ ካሰሩኝ በኋላ ግን በራሴ ላይ የማደርገውን ቅድመ-ምርመራ በማቆም በግልጽ ሙዚቃዬ ላይ የምፈልገውን መልዕክት ማስተላለፍ ጀመርኩ፡፡ ሙዚቃዬ ከተለቀቀ ከአንድ ሰዓት በኋላ ከአካባቢው አስተዳዳሪ ሊያስሩኝ እንደሆነ ስለተነገረኝ ቤቴን ጥዬ ሸሸሁ ከዚያም በኋላ ተመልሼ አላውቅም፡፡

በጃንዋሪ 2016 ዓ.ም. አንድ ኢትዮጵያ ደህንነት ባለስልጣን ለሂውማን ራይትስ ወች በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ሰዎች መከታተል የመንግስት ፖሊሲ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ “የተከበሩ ኦሮሞዎች ላይ የተለየ ትኩረት ማድረግ ጠቃሚ ነው” ብሏል፡፡ ”እንደ በቀለ አይነቶቹን ጨምሮ ከከፍተኛ ደረጃ እስከ መምህራን፣ ተቀባይነት ያላቸው ተማሪዎች እና ኦሮሞ አርቲስቶችን ጨምሮ ማንኛውም ኦሮሞዎችን ማስተባባር የሚችል ሰው የተለየ ትኩረት ይደረግበታል፡፡”

ሂውማን ራይትስ ወች በ2014 ዓ.ም. ታስረው የነበሩ እና ቆይተው የተለቀቁ መልሶም ከእንደገና በቅርቡ በኖቬምበር 2015 ዓ.ም. ተቃውሞው ሲጀመር ወዲያው ታስረው የነበሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን ቃለ-መጠይቅ አድርጓል፡፡ የተወሰኑት በእስር ቤቶች ያለውን ዘግናኝ አያያዝ ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ የነበረው ዋይሲራ እንዳለው፡

(በ2014 ዓ.ም.) ለሁለት ሳምንታት ያህል ታስሬ ነበር፡፡ በፓንት ብቻ ሆኜ ራቁቴን እንድቆም ተደርጌ በዱላ ይደበድቡኝ ነበር፡፡ በጀርባየ ላይ የኤሌክትሪክ ገመድ አስረዋል፡፡ ኦነግ እንደሆንኩ እንዳምን እና ከኦነግ ጋር ነው ብለው የጠረጠሩት ወንደሜ ኦነግ ጋር እንደሆነ እንዳምን ነበር የፈለጉት፡፡ ከጊዜ በኋላ ተፈታሁ፡፡ ወደ ትምህርት ቤት ተመልሼ እንድሄድ አልተፈቀደልኝም፤ ስለዚህ ምንም ሳልሰራ ቁጭ ብየ ነበር የምውለው፡፡ ቤተሰቦቼ ወደሚገኙበት መንደር ተመለስኩ፡፡ በኦሮሚያ ተቃውሞው እንደገና ሲጀመር ያለሁበት ቤት ድረስ መጥተው ከእንደገና አሰሩኝ፡፡ በአካባቢው ምንም አይነት ተቃውሞ አልነበረም ነገር-ግን ቀድሞ በነበርኩበት እና በታገድኩበት ዬኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ተቃውሞ ተነስቶ ነበር፡፡ ተማሪዎቹን በማነሳሳት ወነጀሉኝ እናም ለሁለት ቀናት ያህል ደብድበውኛል፡፡ ከዚያም ከእስር ተፈታሁ፡፡ ምናልባት ተቃውሞ ለማስነሳት ያስባሉ ብለው የገመቷቸውን ማንኛውንም ሰዉ ላይ ትኩረት አድርገው ነበር፡፡

በእስር ቤቶች ማሰቃየት እና ያልተገባ አያያዝ

ሁሉም ቃለ-መጠይቅ ተደርጎላቸው የነበሩ ታስረው የነበሩ ተማሪዎች በተቃውሞው ጀርባ ማን እንዳለ እንዲገልጹ እና ስለቤተሰባቸው ታሪክ ተጠይቀው እንደነበረ ገልጸዋል፡፡ ተማሪዎቸሁ እንዳሉት መርማሪዎቸሁ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ወንጅለዋቸዋል - በዋናነት በህግ ከተመዘገበው የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ እና ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር ጋር ግንኙነት አላችሁ ብለው ነው የወነጀሏቸው፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ለዲያስፖራ ዓለም ኣቀፍ መገናኛ ብዙሃን መረጃ አቀብላችኋል ተብለው በመርማሪዎች የተወነጀሉ ሲሆን በርካታ ቁጥር ያላቸው የተማሪዎች ስልኮች፣ የፌስቡክ ገጽ፣ እና ኢሜይል አድራሻ በታሰሩባቸው ወቅቶች ተመርምረዋል፡፡ እነዚህ መርማሪዎችን በተመለከተ የተደረጉ ማብራሪያዎች ሂውማን ራይትስ ወች ለበርካታ ዓመታት ኦሮሚያን በተመለከተ ከመዘገባቸው መረጃዎች ጋር ተመሳሳይነት አላቸው፡፡

በአዳማ ኒቨርሲቲ መጀመሪያ ዓመት ተማሪ ሆነው ቶሎሳ የሚከተለውን ብሏል፡

ከተቃውሞው በኋላ ምሽት ላይ ነበር፤ በወቅቱ ከነበረው አስለቃሽ ጭስ እያገገምን ባለበት ወቅት እና በተቃውሞው ወቅት ማን በጥይት ተመቶ እንደነበር ለመለየት ጥረት በምናደርግበት ወቅት ነው የጸትታ ሃይሎች የማደሪያ ቦታችንን ያጥለቀለቁት፡፡ እኔ ካለሁበት ቦታ 17 የምንሆን ተማሪዎችን አይናችንን ካሰሩን በኋላ ለሁለት ሰዓታት ያህል በመኪና ከከተማ ውጭ ይዘውን ተጓዙ፡፡ ለዘጠኝ ቀናት ያህል ስራው ያላለቀ አዲስ ህንጻ ውስጥ አስቀመጡን፡፡ ሁልጊዜ ማታ ማታ አንድ በአንድ ይዘውን እየወጡ በዱላ ይደበድቡን እና ይገርፉን ነበር እንዲሁም ከተቃውሞው ጀርባ ማን እንዳለ እና የኦነግ አባላት ስለመሆናችን ይጠይቁናል፡፡ እኔ ኦነግ ማን እንደሆነ እንኳ እንደማላውቅ እና ህዝብን በዚህ መልኩ ማሰቃየት ግን ሁሉንም ወደ ኦነግ ጎራ እንዲቀላቀሉ እንደሚያደርግ ነገርኳቸው፡፡ ይኼንን ስላልኩ በሃይል ደበደቡኝ፡፡ ሙሉ ሌሊቱን የስቃይ ድምጽ ስንሰማ እናድራለን፡፡ ወደ መጸዳጃ ቤት ስንገባ ተማሪዎች በወገባቸው ተንጠልትለው ኮርኒስ ላይ ታስረው እየተገረፉ አይቻለሁ፡፡ አንድ መቶ የሚሆኑ ተማሪዎችን አይቻለሁ፡፡ መርማሪዎቹ ከእኛ አካባቢ አልነበሩም፡፡ አማርኛ እንድንናገር ያስገድዱን ነበር (የሃገሪቱ ብሔራ ቋንቋ)፡፡ ኦሮምኛ ስንናገር ይበሳጩ እና ይደበድቡን ነበር፡፡

በ20ዎቹ እድሜ ክልል የምትገኘው መቲ በምስራቅ ወለጋ ተቃውሞ ከተካሄደ ከአንድ ቀን በኋላ የኦሮሞ ባህላዊ አልባሳትን ስትሸጥ ተገኝታ በዲሰምበር ወር መጨረሻዎቹ አካባቢ ታስራ ነበር፡

ታስሬ ለአንድ ሳምንት ያህል በፖሊስ ጣቢያ እንደቆይ ተደርጌያለሁ፡፡ ሁልጊዜ ማታ ማታ ጎትተው ያወጡኝ እና በደረቅ እንጨት እና በባለጎማ ብትር ይደበድቡኝ ነበር፡፡ ከዚያም ወደ ሌላ ቦታ ወሰዱኝ (ቦታው ያልተገለጸ)፡፡ ለብቻየ አስረው አቆዩኝ፡፡ በተለያዩ ሶስት አጋጣሚዎች ልብሶቼን እንዳወልቅ ተገድጄ በፖሊስ መኮንኖቹ ፊት እንድንቀሳቀስ የተደረኩ ሲሆን ከኦነግ ጋር ስላለኝ ግንኙነት ይጠይቁኝ ነበር፡፡ ተቃውሞውን በማደራጀት በኩል ተባባሪ እንደነበርኩ ካላመንኩ ሊገሉኝ እንደሚችሉ ያስፈራሩኝ ነበር፡፡ ለምን የኦሮሞ አልባሳትን እና ጌጣጌጦችን እሸጥ እነደነበር ጠይቀውኛል፡፡ የማካሂደው ንግድ በኦሮሞነት ከመኩራት የመነጨ መሆኑን ነግረውኝ ሰዎችም ወደ አደባባይ ለሰልፍ የሚወጡት በዚኼው ምክንያት መሆኑን አስታወቁኝ፡፡ በመጀመሪያ በጨለማ ክፍል ውስጥ ነበርኩ፤ ከዚያም በተቃውሞው ወቅት ታስረው ወደነበሩ ሌሎች ሴቶች ጋር ተቀላቅዬ ቆየሁ፡፡

በቦረና ዞን ውስጥ የምትገኝ አንድ የ22 ኣመት ሴት ለሂውማን ራይትስ ወች እንደገለጸችው በዲሰምበር ወር ማገባደጃ አካባቢ ተቃውሞ በተደረገበት እለት ምሽት ታስራ ነበር፤ እናም የወታደራዊ ካምፕ እንደሚመስል በገለጸችው ቦታ ተወስዳለች፡፡ ብቻዋን ሙሉ ለሙሉ ጨለማ በሆነ ቦታ ታስራ ቆይታለች፡፡ ለሁለት ሳምንታት በዚህ ሁኔታ በቆየችባቸው ወቅቶች ባልታወቁ ሰዎች ለሶስት ጊዜያት ተደፍራለች፡፡ በየአንድ አንዱ አጋታሚ ሁለት ሁለት ሰዎች እንደነበሩ ገልጻለች፡፡ በተደጋጋሚ ከታሰረችበት ክፍል ተጎትታ እየወጣች በተቃውሞው ላይ ያላትን ተሳትፎ ትጠየቅ ነበር፤ ሁለቱ ወንድሟቿ ያሉበትንም አድራሻ ይጠይቋታል፤ መርማሪዎቹ ወንድሞቿ የተማሪዎችን አመጽ እየቀሰቀሱ እንደሆነ ወንጅለዋቸዋል፡፡ ሁለቱን ወንድሟቿን ለጥያቄ ወደ ጸጥታ ሃይሎቹ እንደምታመጣቸው ቃል በመግባት በቅድመ-ሁኔታ ተፈታለች፡፡

የጤና እና የትምህርት አገልግሎት የማግኘት መብት

ባለስልጣን አካላቱ የጤና ባለሙያ ሰራተኞችን ለማሰር ልዩ ትኩረት አድርገውባቸዋል በዚህም ምክንያት የተወሰኑ የቆሰሉ ተቃውሞ አድራጊዎች የህክምና እርዳታ ማግኘት አልቻሉም፡፡ በምስራቅ ወለጋ ተማሪ የሆነው ደመቅሳ እንደገለጸው በዲሰምበር ወር ማገባደጃ ላይ የኦሮሚያ ክልላዊ ፖሊስ በተቃውሞ አድራጊዎች ላይ በተኮሰው አስለቃሽ ጭስ ምክንያት እና ተገፍቶ በመውደቁ በክንዱ እና ፊቱ ላይ ለደረሰበት ጉዳት የህክምና እርዳታ ማግኘት ተከልክሏል፡፡ “እነሱ (የጤና ባለሙያዎቹ) እንዳሉት እኔን ማከም አይችሉም፡፡ ከአንድ ቀን በፊት የጸጥታ ሃይሎች ሁለት የስራ አጋሮቻቸውን በተቃውሞ ላይ ለነበሩ ሰዎች የህክምና እርዳታ ስላደረጉ አስረዋቸዋል፡፡ ለተቃዋሚዎች የጤና አገልግሎት ሽፋን በመስጠት በሚል ተወንጅለዋል፡፡”

የተቃውሞው ምልክት የሆነውን ሁለት እጃቸውን ከራስ በላይ ከፍ አድርጎ ክንድ እና ክንዳቸውን በመስቀለኛ መንገድ በማጣመር ፎቶ ተነስተው በፌስቡክ ማሕበራዊ ደረ-ገጽ በመልቀቃቸው ምክንያት የጸጥታ ሃይሎች እንዳስፈራሯቸው እና እንዳሰሯቸው የጤና ባለሙያዎች ገልጸዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ የሚገኝ አንድ የጤና ባለሙያዎች እንደገለጸው በርካታ ተማሪዎች በጥይት ተመተው ከፍተኛ እርዳታ በሚስፈልጋቸው ወቅት የአንድ ወታደር አነስተኛ ጉዳትን እንዲያክም ጠመንጃ ደቅነው አስገድደውታል፡፡ በዛው እለት ምሽት ቢያንስ አንድ ተማሪ በደረሰበት ጉዳት ሳቢያ እንደሞተ የጤና ባለሙያው ተናግሯል፡፡

በርካታ ተማሪዎች እንዳሉት የአካባቢው ባለስልጣናት ትምህርትቤቶችን እንዲዘጉ ያደረጉ ሲሆን ኼውም ተማሪዎቹ ለተቃውሞ እንዳይደራጁ ለመከላከል ነው፤   አሊያም መምህራኑ ስለታሰሩ ሊሆን ይችላል፡፡ የተወሰኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ክፍላቸው ለመሄድ ስጋት ያለባቸው እንደሆነ ሲገልጹ ወደ ትምህርትቤት አለመሄድ ደግሞ በመንግስት ላይ ተቃውሞን መግለጫ መንገድ አድርገው የወሰዱትም አሉ፡፡ ታስረው የነበሩ አራት ተማሪዎች እንደገለጹት የጸጥታ ሃይሎች ወደ ኒቨርስቲዎቻቸው እንዲመለሱ እንማይፈቅዱላቸው ነግረዋቸዋል፡፡ የ 6ተኛ ክፍል ተማሪ የሆነች ታዳጊ ልጅ እንደገለጸችው በትምህርት ቤቷ ከፍተኛ የተባለውን ውጤት ያስመዘገበች ቢሆንም የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ በተቃውሞ ሰልፉ ስለተሳተፈች ወደ ትምህርትቤቷ እንድትመለስ ሊፈቀድላት እንደማይችል ነግረዋታል፡፡ በዚህም ምክንት ከኢትዮጵያ ለቃ ለመውጣት ወስናለች፡፡

ሂውማን ራይትስ ወች ከዚህ በፊት በ2014 ዓ.ም. ተቃውሞ ተሳትፈው የነበሩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው እንዳይመለሱ መደረጉን በተመለከተ መረጃዎችን ሰብስቦ አስቀምጧል፤ ይህ አሰራር አሁን ባለው ተቃውሞ ማግስት ተግባር ላይ እየዋለ የሚገኝ ሆኖ ቀጥሏል፡፡

Your tax deductible gift can help stop human rights violations and save lives around the world.

Region / Country